ሴቶችን በኢኮኖሚ የማጎልበት ተግባር ላይ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ ድህነትን ለመቀነስ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። ሴቶች በንግድ ስራ፣ በእርሻ፣ በስራ ፈጠራ ወይም በተቀጣሪነት ብሎም በቤት ውስጥ በሚከውኗቸው በገንዘብ የማይተመን ስራ ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ይስተዋላል። ሆኖም በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች ሴቶች ለበርካታ ዓይነት መገለሎች እንደሚዳረጉ እና በኑሮ ስርዓታቸው ላይ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በሚያደርሱት አሉታዊ ተፅእኖዎች ተቀዳሚ ተጠቂ እንደሚሆኑ ይነገራል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ከሴቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ቢኖሩም፣ ችግሩ በከተማም ሆነ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ሥር የሰደደ ጉዳይ ሆኗል። ይህም ጎልቶ የሚታየው እንደ ምዕራብ ኦሞ ዞን ባሉ የገጠር አርብቶ አደር አካባቢዎች እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

የኃይለማሪያም እና ሮማን ፋውንዴሽን በ2013 ዓ.ም በምዕራብ ኦሞ ዞን ባደረገው ዳሰሳዊ ጥናት ሴቶች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ ከሚያደርጋቸው ተግዳሮቶች መካከል በአከባቢው ያለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ዋንኛው ሲሆን በተለይም ማህበረሰቡ ሴቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የስራ ጫና የሚያሳድርባቸው እና ሴቶች ገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ በመሳተፍ የሀብት ባለቤት እንዳይሆኑ ተጽኖ የሚፈጥርባቸው እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ፋውንዴሽኑ የችግሩን አንገብጋቢነት በመረዳት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የአድቮከሲ ኮንፍራንሶችን በማዘጋጀትና የሴት አርብቶ አደሮችን የመነሻ ካፒታል ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።  በዚህ መሰረት ፋውንዴሽኑ ከምዕራብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር ዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴት አርብቶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ተግባር ገብቷል። በዚህም በባለፈው ዓመት በዞኑ ከሚገኙ መኢኒት ሻሻና መኢኒት ጎልድያ ወረዳዎችን ጨምሮ ከአንድ የከተማ አስተዳደር እና አራት ቀበሌዎች ለተውጣጡ 62 ሴቶችና ወጣቶች የስራ ፈጠራና የንግድ ክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በማህበር እንዲደራጁ ተደርጓል።  በዚህ ኢኮኖሚያዊያዊ አቅም ማጎልበት ፕሮጀክቶች 62 ተጠቃሚ አርብቶ አደሮች በ7 ማህበራት የታቀፉ ሲሆን ፋውንዴሽኑ 372,000 ብር የመነሻ ገንዘብ በመመደብ በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ አማካኝነት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን እና የመኢኒት ሻሻና መኢኒት ጎልድያ ወረዳዎች የመንግስት መዋቅር ማህበራቱን ከማደራጀት ጀምሮ የማህበራቱን የስራ እንቅሰቃሴ በመከታተል ረገድ ከፋውንዴሽኑ ጋር በቅንጀት በመስራት ላይ ይገኛል። በመኢኒት ሻሻ ወረዳ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎና ማስፋፊያ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ክብነሽ ለገሰ በሰጡን አስተያየት “ሴት አርብቶ አደሮች ኋላ ቀር በሆኑ አመለካከቶችና የኢኮኖሚ አቅም በማጣታቸው ሕይወታቸው ላይ ተጽንዎ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠት እንደማይችሉና ጾታ ላይ ለተመሰረቱ ጥቃቶች ሰለባ ይሆናሉ፤” ሲሉ  ይናገራሉ። ለችግሩ መፍትሄ ሲሉ በሰጡት አስተያየት ሴቶችን ጨምሮ ወንድ አርብቶ አደሮችን ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን መፍጠርና ሴት አርብቶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጎለብት የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራትን ማመቻቸት የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገር ለጥቃት የሚጋለጡበትን ሁኔታ ይቀንሳል በማለት ሃሳባቸውን ያጋሩን ሲሆን የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን የችግሩን ጥልቀትና አንገብጋቢነት በመረዳት እያደረገ የሚገኘውን አስተዋጽዎ በማድነቅ በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ ባመቻቸው ፈንድ በማህበር ተደራጅተው ገቢ ማስገኛ ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ ሴት አርብቶ አደሮች መካከል በጀሙ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አስካለች መለሰ አንዷ ስትሆን እርሷን ጨምሮ ስምንት አባላትን በያዘው ማህበር በበግ ማድለብ የንግድ ዘርፍ ተሰማርታ ትገኛለች። ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ አስካለች በዚህ ማህበር ተደራጅታ ከስምንት ወራት በፊት ስራ ከመጀመሩዋ አስቀድሞ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ የሌላት እና በባለቤትዋ ገቢ ብቻ የምትተዳደር እንደነበረች ትናገራለች። በአሁኑ ሰዓት በምታገኘው ገቢ ልጆቿን ከማስተማር ባሻገር የቁጠባ ባህል በማዳበር በየጊዜው ተቀማጭ እንደምታደርግ እና በቀጣይ ታህሳስ ወር ለገበያ የሚቀርቡ በጎችን ማህበሩ ያሰናዳ መሆኑንና በሚገኘው ትርፍ  ተጨማሪ በጎችን ለመግዛት  እቅድ እንዳላቸው በመናገር የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ላደረገላቸው አስተዋጽዎ በማህበሩ ስም ምስጋና አቅርባለች።

ሌላኛው የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ፕሮጀክት ተጠቃሚ አቶ የማታወርቅ ታደለ በመኢኒት ሻሻ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከመሰል ስራ አጥ ጓደኞቹ ጋር ማህበር መስርተው ፋውንዴሽኑ ባመቻቸው የገንዘብ ድጋፍ በወጣት ማዕከል የመዝናኛ እና ሻይ ቡና አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ወጣት የማታወርቅ እና የስራ ባልደረቦቹ በዚህ የገቢ ማስገኛ ተግባር ላይ ከመሰማራታቸው በፊት ምንም ዓይነት ስራ ያልነበራቸውና አልባሌ ቦታ የሚያሳልፉ እንደነበር የኋላ ታሪኩን ያጫወተን ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ባበረከተላቸው የ72,000 ብር ድጋፍ የዲ.ኤስ.ቲቪን ጨምሮ በካፍቴሪያ አገልግሎት ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን ይናገራል።  ከዚህ ጎን ለጎን የፋውንዴሽኑን ልገሳ መነሻ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከሉን ያለምንም ክፍያ እንዲጠቀሙ ማመቻቸቱን ወጣት የማታወርቅ ጠቁመዋል።

ኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን
ጥቅምት 2015፣ ምዕራብ ኦሞ